The speach made by first hijar during the protest march 20/2009

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩኅ አዛኝ መሃሪ በሆነው።እኛ ኢትዮጵያውያን አብሮ ባኖረን አብሮ በሚያኖረን ቃል-ኪዳን ተሳስረናል። ይህንን እፁብ ድንቅ የሆነ ቃል-ኪዳን ጠብቀን ለቀጣዩ ትውልድ እንደምናስተላልፍ ስንገልጽ ታላቅ ደስታ ይሰማናል። ስለምን ቢባል የምንከተለው ሐይማኖትኢስላም- ተቻችሎ የመኖር ቃል-ኪዳንን በፅኑ ያስተምረናልናነው። ድህነት፣ የተፈጥሮ ችግር፣ ረሃብና በሽታ በሚፈራረቁባት ውዷ እናት አገራችን ላይ እንደማንኛውም ዜጋ የሚደርሰውን ችግር ብንጋፈጥም፣ እንደማንኛውም ዜጋ ችግሩን ብንጋራም ሙስሊም ሆኖ በምድረ-ኢትዮጵያ መኖር ተጨማሪ ችግር እንዳለው፤ ተጨማሪ ችግር እንደነበርው ከታሪካችን ማህደር ልንፍቀው ከዘመኑ የኑሮ ተሞክሮ ልናገለው የማንችለው አሳፋሪ የታሪካችንና የህይወታችን ገፅታ ቢሆንም በኢትዮጵያዊነታችን እንደማንኮራ ስንገልጽ ልባዊ ደስታ ይሰማናል። ኢትዮያዊ ሙስሊም ሆኖ መኖር ፈታኝ ቢሆንም ይንን ፈተና የሚያቀናጁት ጥቂት ጨቋኝ ኃይላትና አክራሪ የሐይማኖት መሪዎች ናቸው። ዛሬ ደግሞ ዓለም በጨቋኞችና በአክራሪዎች የተንገፈገፈች በመሆኗ፤ እኛም ዛሬ እዚህ ቆመን ለጨቋኞችና ለአክራሪዎች «በቃችሁ አትበጥብጡን- አታበጣብጡን» በማለት ፅናት የተሞላበትን ወደፊት እንጂ ወደኃላ የማንመለስበትን ሰላማዊ ድምፃችንን በወኔ እናሰማለን። ተንኮል በፍቀር ይሸፈናል። ለዘመናት እንድንተላለቅ ሲዶለትብን፤ ፍቅርን ተጋርቶ ፍቅርን ላጋራን፣ ከሰላም ተዋውሎ ሰላምን ላዋዋለን፣ በባህል በዘር በጋብቻ በልቅሶ በሰርግ በወሊድ ወቅት እንደተቆራኘው ሁሉ ለተቆራኘን፤ ውድ ለሆነው ኢትዮጵያዊው ህዝበ-ክርስቲያን ያለንን አክብሮት እየገለጽን ነገም በዚሁ ሰላማዊ የአኗኗር ዘይቤ ከክርስቲያን ወገኖቻችን አብረን እንደምንኖር በደስታ እንገልፃነን። እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር 1966 ባደረግነው ታላቅ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በአዲስ አበባ ጎዳኖች ድምፃችንን ከፍ አድርገን ያስተጋባንነው በልቦናችንንና በአንደበታችን የዘመርነው የቃል-ኪዳን ተምሳሊት የማንነት ምልክት የሆነ መፈክር ነበር ዛሬም 35 ዓመት በኋላ እንደግመዋለን።ኢትዮጵያ አገራችን! ክርስቲያን ወንድማችን! ይመስክር ደማችን! አንድ ነው እጣችን!!” አንድ ህዝብ በመሆናችን አንድ እጣ ነው ያለን! አንድ ህዝብ በመሆናችን አንድ ተስፋ ነው ያለን። የኢትዮጵያ ህዝብ በዘር በብሔር በሐይማኖት ቢለያዩም እንደ አንድ ገላ ነው። የሙስሊሙ መጎዳት፣ የሙስሊሙ መጎሳቆል፣ የሙስሊሙ ሰብዓዊ መብት መገፈፍ የክርስቲያን ወገኑም ሆነ የሌላው የጋራ ችግር ነው። ፍቅርን ባስተማሩን ኢየሱስ (..) ርኅራኄን ባስተማሩን ሙሐመድ (...) የጽድቅ መንገድ በህብረት ተሰማርተን ይህንን መጤ የጭቆና አመራርና በሐይማኖት ስም ስውር የፖለቲካ ዓላማ ያለውን ፅንፈኝነትን በጣምራ ሳይከፋፍሉን፣ ሳያጫርሱን፤ በፍቅር በአንድነትና በሰላም አጥምደን ይዘናቸው የሰብዓዊነትን ሁለንተናዊ ሰንደቅ ከፍ አድርገን እናውለበልብ። ይህ ሰላማዊ ሰልፍ የሰላም ጥሪ ነው። ይህንን የሰላም ጥሪያችንን የሰሙ ኢትዮጵያዉያን ሁሉ የጋር ለሆነችዋ አገር ህልውና ቅድሚያ በመስጠት በሰላምለሰላም እጅለጅ ተያይዘው በአንድነትና በልማት ወደኋላ ያስቀሩንን ጭቆናና በሐይማኖት ሽፋን የሚከናወነውን ዘልማዳዊ የአሰራር ዘይቤ የጥፋት እንጂ የልማት ተምሳሊት ባለመሆናቸው በቃችሁ፤ ኢትዮጵያ ልማት እንጂ ጥፋትን አትሻም እንበላቸው። የዛሬን የሰላም ድምፃችንን ለማዳፈን ከዓይናችን እይታ ዘወር ብለው ተበታትነውም ይሁን ተሰባስበው በመዶለትና በማስዶለት፤ በማደምና በማሳደም በሐይማኖት ስም ስውር የፖለቲካ ዓላማን የሚያራምዱ ወገኖች ይህንኑ የሰላም ጥሪያችንን ሰላማዊ ዓላማን በማጣመም የራሳቸውን ጥፋት በኛ በሰላም ፈላጊዎቹ ላይ በማላከክ በሐይማኖት ስም የፖለቲካ ቅዠት በመቃዠት ስለማይቆጠቡ አብሮ ባኖረን አብሮ በሚያኖረን ሰላም ፍቀር ተቻችለን እንኖራለን እንጂ በቅዠት አንመራም እንበላቸው። እነዚህ በእምነት ስም የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው ፀጉር ልውጦች በየእምነት ማዕከሉ፣ በየማህበራቱ፣ በየሰው ቤት ካሊያም በየአደባባዩ ዓላማቸውን ለማሳካት እንደ ጥላ ስለሚከለሉን እምነትን የግል አገርን የጋራ አድርገን ለመከፋፈል ቦታ የለም! ለፀብ አጫሪነት ቦታ የለም! ለጭቆና ቦታ የለም! — እንበላቸው!! አብሮ ያኖረን አብሮ የሚያኖረን ቃል-ኪዳን አይታጠፍም። ኢትዮጵያዉያን በአንድነት እንኖራለን! ኢትዮጵያዉያን ተቻችለን እንኖራለን! ኢትዮጵያዉያን በሰላም እንኖራለን! ይሔ ቃላችን ነው፤ ይሔ ተስፋችንአላህ ይርዳን። አሚን!! አመሰግናለሁ። (ከፈርስት ሂጅራ የሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪ ኮሚቴ)